ከምርመራ መዛግብት…
በሀሰተኛ ሰነድ የከተማ ቦታ ያጭበረበረው ግለሰብ ተቀጣ
ከፖሊስ መደበኛ ተግባራት መካከል የፖሊስ ጥበብ፣ ብስለት፣ ብልጠትና አስተዋይነት የሚስተዋልበት የሙያ ዘርፍ ነው የወንጀል ምርመራ።
ወንጀለኛ መረጃና ማስረጃ ለማግኘት ግልፅና ቀላል ከሆኑ የወንጀል ተግባራት እስከ ስውር እና ውስብስብ ወንጀሎች ሲፈጸም የወንጀል መርማሪ ፖሊስ ለወንጀሎች መረጃና ማስረጃን በብስለትና በጥበብ አፈላልጎ፣ አውጣጥቶ በወንጀል ፈፃሚው ላይ ህጋዊ የፍትህ ስርዓት እንዲተገበር በማድረግ የተበዳዮችን እምባ በማበስ ኀላፊነቱን ይወጣል።
በአማራ ክልል የምዕራብ ጎጃም ዞን መቀመጫ ወደሆነችው ፍኖተሰላም ከተማ ተጉዘን በከተማዋ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ሀሴትን እና በፖሊስ የምርመራ ስራ ላይ ያላቸውን እምነት ያጎለበትን አንድ የወንጀል ምርመራ ታሪክን እንዲነግሩን ከዞኑ ፖሊስ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዋና ክፍል ኃላፊ ከሆኑት ኮማንደር አስማረ አሊ ጋር ቆይታ አድርገናል።
በፍኖተ ሰላም ከተማ ከህገወጥ የመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ አንድ ግለሰብ ከመንግሥት 250 ካሬ መሬት ለመኖሪያ ቤት መስሪያ ተቀብሎ ሳለ በህገ-ወጥ መንገድ ሀሰተኛ ካርታ በማሰራት 29,982 ካሬ ሜትር ነው በማለት ለማጭበርበር ሞክሯል።
ግለሰቡም በአካባቢው ማህበረሰብ ቅሬታ ሲቀርብበት እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዘለቀ የፍትሐ-ብሔር ክርክር በማድረግ ባቀረባቸው ሀሰተኛ የካርታ ማስረጃዎች አሳምኖ መሬቱን ለግሉ አድርጎም ነበር።
እውነቱን የሚያውቁት የከተማዋ ማህበረሰብም ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ተቃውሞ መደረጉን ኮማንደር አስማረ አሊ ያስታውሳሉ።
የህዝብን ጥያቄ መሰረት በማድረግም ጉዳዩ ለፖሊስ ተሰጥቶ በአዲስ ምርመራ ሲደረግም ከከተማ አስተዳደሩ ፋይናንስ ቢሮ በተገኘ የሰነድ ማስረጃ እንዲሁም የሰው ማስረጃ የግለሰቡ ህጋዊ ቦታ 250 ካሬ ሜትር ብቻ ሆኖ ቀሪው የውሸት ካርታ የተዘጋጀለት ሆኖ መገኘቱን ፖሊስ በምርመራ ማረጋገጡን ኮማንደር አስማረ ገልጸዋል።
በመሆኑም ጉዳዩ በፍጥነት ተጣርቶ ክስ ተመስርቶ ግለሰቡን በ8 ዓመት ከ5 ወር አእስራት እንዲቀጣ እና በማጭበርበር ለግል ጥቅሙ አውሎት የነበረው መሬትም ለመንግስት እንዲመለስ ተወስኖበታል።
የከተማዋ ማህበረሰብ በፖሊስ ደስተኛ የሆነበትና አመኔታን ያሳደረበት ምርጡ የወንጀል ምርመራ ነበር ሲሉ ኮማንደር አስማረ አሊ ተናግረዋል።
ኮማንደር አስማረ አሊ አክለውም ወቅቱ ማስረጃ እና ምስክር ለማግኘት አሰጋቸሪ ቢሆነም በዚህ በጀት ዓመት ከ250 በላይ የምርመራ መዝገቦችን አጣርተናል አሁንም መደበኛ የወንጀል ምርመራ ስራችን በተገቢው መንገድ እየከወነ እንገኛለን ብለዋል።

