“ዞኑ ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር በመቀልበስ ሰላም ማስፈን ተችሏል።” አቶ እድሜዓለም አንተነህ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ

“ዞኑ ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር በመቀልበስ ሰላም ማስፈን ተችሏል።” አቶ እድሜዓለም አንተነህ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ

በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት ጥቁር ጥላ ካጠላባቸው አካባቢዎች መካከል የምዕራብ ጎጃም ዞን አንዱ እንደነበር የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እድሜዓለም አንተነህ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለፃ በዞኑ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ የነበረበት፣ የግልና የመንግስት ንብረቶች የተዘረፋበት፣ የወደሙበት እና ተቋማት የተዘጉበት በዚህም ማህበረሰቡ የተንገላታበት ወቅት ነበር።

አሁን ላይ ማህበረሰቡን በማሳተፍ በክልሉና በፌደራል የፀጥታ አካላት ጥምረት እና ልዩ ጥረት የነበረውን የፀጥታ ችግር በመቀልበስ አንፃራዊ ሰላም ማምጣት ተችሏል ብለዋል።

ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የህብረተሰቡን አጋርነት ከጸጥታ መዋቅሩ ቁርጠኝነት ጋር በማቀናጀት በዞኑ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ክንዴ ብርሀን በበኩላቸው የፀጥታ ችግሩ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ማህበረሰቡ በርካታ ችግሮችን አሳልፏል።

አሁን ላይ የክልሉ የፀጥታ ኀይል ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ባደረገው ብርቱ የሰላም ማስከበር እና የወንጀል መከላከል ተግባር በዞኑ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል።

በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች መደበኛ የፖሊስ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል የሚሉት ኮማንደር ክንዴ ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር አሁን ያለውን ሰላም ለማስቀጠል እየሰሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

ፖሊስ ከማህበረሰቡ፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከወጣቶች ጋር በመሆን ጥበቃን በማጠናከር እና ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ ፍትህ እንዲረጋገጥ እየተደረገ ይገኛል ያሉት ኮማንደር ክንዴ አሁን ላይ ይፈፀሙ የነበሩ ወንጀሎች እና ህገ-ወጥ ድርጊቶች መቀነሳቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች በህገ-ወጥ መንገድ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው እጅ አየሰጡ ይገኛሉ።

ሌሎች ታጣቂ ኃይሎችም የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ኮማንደር ክንዴ ብርሀን ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top