በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የታጣቂ ቡድን አመራሮች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመለሱ
በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድን አመራሮች እና አባላት፣ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ሙሉ ትጥቃቸውን አስረክበው ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸው ተገለጠ።
ወደ ሰላም ከተመለሱት የቀድሞ የታጣቂ ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ቢኒያም አስፋው – የቡድኑ አደረጃጀት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ አየነው አስፋው – የኮር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ አብረሀም አስማረ – ሻለቃ ዘመቻ እንዲሁም መንገሻ ነበሩ – ሻምበል መሪ ይገኙበታል።
ታጣቂዎቹ መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ያቀረበውን የይቅርታ ጥሪ መሠረት በማድረግ፣ ከነሙሉ ትጥቃቸው ለመንግሥት እጃቸውን ሰጥተዋል።
ቡድኑ ላለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ ውስጥ የልማት ሥራዎች እንዲስተጓጎሉ ሲያደርግ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፣ አመራሮቹ በፈጸሙት ተግባር በመጸጸት የቀረበላቸውን የምህረት ዕድል ለመጠቀም መወሰናቸው ተነግሯል።
የአካባቢው የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መመሪያ፤ ወደ ሰላም የተመለሱት ግለሰቦች በቀጣይ በልማት ሥራዎች ላይ በንቃት በመሰማራት፣ ቀድሞ የበደሉትን ሕዝብ በሥራቸው ሊክሱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
መንግሥት የዘረጋውን የሰላም እጅ ተጠቅሞ ወደ ሰላማዊ መንገድ መመለስ ብልህነት ነው፤ ቀጣዩ ምዕራፍ ሕዝብን የመካሻ እና የአካባቢውን ልማት የማፋጠኛ ጊዜ ይሆናል።
በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ኃይሉ ከሕዝቡ ጋር ያለውን ቅንጅት በማጠናከር፣ በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና የሕግ ማስከበር ግዳጁን በስኬት እየተወጣ እንደሚገኝ ታውቋል።





