የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ከሌሎች የፀጥታ አካላት እና ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት ከተማዋን ከወንጀል ስጋት ነፃ የማድረግ ስራን እያከናወነ ይገኛል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ከሌሎች የፀጥታ አካላት እና ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት ከተማዋን ከወንጀል ስጋት ነፃ የማድረግ ስራን እያከናወነ ይገኛል።

ፖሊስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በተለይ በከተማዋ ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እና የቱሪስትና የንግድ እንቅስቃሴው እንዳይስተጓጎል ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው።

የታሪካዊቷ የጎንደር ከተማን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ዘመናዊ አሰራሮችን ከማህበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ ጋር በማቀናጀት ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አንተነህ ቴወድሮስ ገልጸዋል።

የጸጥታ ኃይሉ በከተማዋ ስልታዊ ቦታዎች ላይ የጋራ የጥበቃና የፍተሻ ስራዎችን በማከናወን የህገ-ወጥ መሳሪያ ዝውውርንና የወንጀል ድርጊቶችን እንቅስቃሴ ገድቧል ሲሉም አዛዡ ጠቁመዋል።

እንደ ኮማንደር አንተነህ ቴወድሮስ ገለጻ ወንጀል ሊፈጸምባቸው የሚችሉ አካባቢዎችን በመለየትና በመቆጣጠር፣ በከተማዋ የሚታዩ የሌብነትና የውንብድና ሙከራዎችን አስቀድሞ የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ጥቃቅን ግጭቶችና አለመግባባቶች ወደ ትልቅ ወንጀል ሳይሸጋገሩ በባህላዊና በማህበረሰብ አደረጃጀቶች እንዲፈቱ በማድረግ የፖሊስንና የፍትህ አካላትን የስራ ጫና ቀንሷል ብለዋል።

ከፍተኛ የህዝብ እንቅስቃሴ በሚኖርባቸው ወቅቶች እና በበዓላት ወቅት፣ ማህበረሰቡ ከትራፊክና ከመደበኛ ፖሊስ ጋር በመሆን በፈቃደኝነት የጥበቃና የሰላም ማስከበር ስራዎችን እንደሚያከናውኑም አዛዡ ጠቁመዋል።

ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት በማጠናከር እና የማህበረሰብ ፖሊስ አገልግሎትን በማስፋፋት ከተማዋን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የየከተማው ፖሊስ ከህዝብ ተሳትፎ ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከክልል አድማ ብተና፣ ከሚሊሻ እና ከደህንነት መዋቅሩ ጋር ተቀናጅቶ በመሰራቱ፣ በከተማዋ ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም የፀጥታ ስጋቶች በወቅቱ ለመቀልበስ አስችሏል ብለዋል።

በጎንደር ከተማ አሁን ላይ የታየው አንፃራዊ ሰላም የፀጥታ ኃይሉ የጥንካሬ ብቻ ሳይሆን፣ የማህበረሰቡና የወጣቶች የተቀናጀ ጥረት ውጤት ነው።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የ4ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የኦፕሬሽናል ንኡስ ክፍል ኃላፊ ዋና ሳጅን የሽዋስ በለጠ በበኩላቸው ማህበረሰቡ በተደራጀ መልኩ በየአካባቢያቸው የሚፈጠሩ ግጭቶችን በማረጋጋት እና ወጣቱን ከአጥፊ ድርጊቶች በመጠበቅ ረገድ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል ።

በመደበኛነት በሚከናወኑ የፓትሮል ስራዎች በተለይም ህዝብ በሚበዛባቸው የገበያ ስፍራዎች እና የቱሪስት መስህቦች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ (Community Policing) ስራው በየቀበሌው ካሉ የሰላም ኮሚቴዎች ጋር በመቀናጀት፣ አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ለፖሊስ በፍጥነት የማሳወቅ ልምድ ዳብሯል ሲሉም ኃላፊው አክለዋል።

ወጣቶችና ተማሪዎች ከወንጀል ድርጊት እንዲርቁ እና ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ በትምህርት ቤቶችና በማህበራዊ ስብሰባዎች ላይ ሰፊ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የአካባቢዬ ሰላም የኔ ነው በሚል መርህ በየሰፈሩና በየቀጠናው ተደራጅተው የሚያደርገው የሌሊት ጥበቃዎች ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ ስራን እያከናወኑ ይገኛሉ ሲሉም አክለዋል።

የከተማችንን ሰላም ለመጠበቅ ከፖሊስ ጎን ቆመን በየሰፈራችን በፈረቃ እያደረግን ያለነው ጥበቃ ሌቦችና ወንጀለኞች የሚንቀሳቀሱበት ቀዳዳ አሳጥቷቸዋል ይላሉ በከተማዋ የሌሊት ጥበቃ ሲያደርጉ ያገኘናቸው ነዋሪዎች።

ወንጀለኞችን አሳልፎ በመስጠትና ለፀጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ደጀንነት በመስጠት የከተማችንን ሰላም የራሳችን የቤት ስራ አድርገን እየሰራን ነው ብለዋል ነዋሪዎቹ።

በየቀበሌውና በየጎጡ በመደራጀት ሌሊትና ቀን አካባቢያችንን በመጠበቅ ለፖሊስ ትልቅ አጋዥ ሆነናል ብለዋል።

በፀጥታ አካላቱ እና በማህበረሰቡ መካከል ያለው የጠነከረ የመረጃ ልውውጥ ማንኛውንም የፀጥታ ስጋት በጋራ ለመመከት አስችሎናል ሲሉም ነዋሪዎች አክለዋል።

ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠትና በሰላም ግንባታ ስራው ላይ ያለንን ተሳትፎ አጠናክረን በመቀጠል ሰላማችንን እንጠብቃለን ሲሉም የከተማዋ ነዋሪዎች አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top