የ2018 ዓ.ም የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ የጸጥታ ዝግጅት ተደርጓል።
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ2018 ዓ.ም የከተራ እና የጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
ጥምቀት የአንድነት፣ የፍቅር እና የሰላም በዓል ነው። ይህ ታላቅ በዓል በክልላችን ሲከበር ከመንፈሳዊ እሴቱ ባለፈ የቱሪዝም እና የወንድማማችነት መገለጫ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ስለሆነም የ2018 ዓ.ም የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በሰላም እና በታላቅ ድምቀት እንዲከበሩ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከፌደራል እና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በዓሉ የሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ለማድረግ ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከፌደራል ደኅንነት አካላት እና ከክልሉ የጸጥታ መዋቅሮች ጋር የጋራ ኦፕሬሽን ማዕከል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።
በተለይም በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ፣ በባህር ዳር፣ በደብረ ማርቆስ፣ በደሴ እና በደብረብርሃን እንዲሁም በሌሎችም የክልሉ ከተሞች ከፍተኛ የሰው ሃይል እና የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ተመድበው ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ይገኛል።
የጥምቀት በዓል በሚከበርባቸው አደባባዮች ዙሪያ አስተማማኝ ጥበቃ ማድረግ፤ የህዝቡን እና የቱሪስቶችን ደህንነት ማረጋገጥ፤ ትራፊክ ፍሰቱ እንዳይስተጓጎል አማራጭ መንገዶችን ማዘጋጀት እንዲሁም ማንኛውንም ትንኮሳና የጸጥታ ስጋት አስቀድሞ መከላከል ላይ ነው የጸጥታ ኃይሉ ቅድመ ዝግጅት በዋናነት ያተኮረው።
በዓሉ የሰላም እንዲሆን የሃይማኖት አባቶች፣ የወጣቶች አደረጃጀቶች እና የከተማ ነዋሪዎች ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅርበት እንዲሰሩ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።
እንግዶችን በመቀበል እና በዓሉን በባህላዊ ጨዋነት በማክበር ረገድ ህዝቡ ልምዱን እንዲደግም ተጠይቋል።
በዓሉ የሰላም፣ የጤና የፍቅር እንዲሆንላችሁ ከልብ እንመኛለን።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ
በጀግንነት መጠበቅ፤ በሰብዓዊነት ማገልገል!

