በቀጣይ የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲፈጸም የፀጥታ ተቋማት ሚና የላቀ ነው
በቀጣይ የሚካሄደው ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዲፈጸም የፀጥታ ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑን “የምርጫ ደህንነትና የፀጥታ ተቋማት ሚና” መጽሐፍ ጸሀፊ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) “የምርጫ ደህንነትና የፀጥታ ተቋማት ሚና” መጽሐፍ ተመርቋል።
በመጽሐፍ ምረቃ ወቅት የጦር `ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት የሃይማኖት አባቶች አባገዳዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባትና የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚቻለው በምርጫ ብቻ መሆኑ ግድ የሆነበት ጊዜ ነው።
ዓለም የደረሰበትን የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት፣ የምርጫ አስተዳደር ስርዓት እና ያንን ሊያናጉ የሚችሉ የአሰራር ግድፈቶችን የሚያርምና የሚቆጣጠር ስርዓት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
ምርጫን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ያከናወኑ ሀገራት ጠንካራ የመንግስት ስርዓት እንደገነቡ አውስተው፤ በተቃራኒው የምርጫ ስርዓታቸውን በአግባቡ ያላከናወኑ ሀገራት ደግሞ ለእርስ በእርስ ግጭትና ለስርዓት አልበኝነት እንደተዳረጉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ዙር ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።
ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዲፈጸም የፀጥታ ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑን አንስተዋል።
መጽሐፉ በቀጣይ የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጥናት ላይ የተመሠረተ ልምድ የሚያጋራ ሲሆን፤ ለፀጥታ አባላትም በእውቀት ላይ ተመስርተው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እገዛ ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል።
ኮሚሽነሩ በስድስቱ ዙር ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎች ላይ ተሳትፎና የፀጥታ ተቋማትን በመምራት ያገኟቸውን በጎ ልምዶችና የታዩ እጥረቶች በመመርመር የተዘጋጀ መጽሐፍ መሆኑንም ተናግረዋል።
መጽሐፉ ለልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆን በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በእንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ እንደተዘጋጀ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታውቋል።






