“ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን የሚጸየፍ እንዲሁም ሙስና የሚሰሩትን ተከታትሎ ለህግ የሚያቀርብ የፖሊስ ሰራዊት መገንባት ይገባል።” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)
‘ትውልድን በስነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር’ በሚል መሪ ቃል ለ22ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ ሙስና ቀን ምክንያት በማድረግ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተከብሯል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ
በመድረኩ ተገኝተው እንደገለጹት የሀገር ኢኮኖሚን ከሚያደቁና እድገትን እያቀጨጩ ከሚገኙ ህገ-ወጥ ተግባራት መካከል ሙስናና ብልሹ አሰራር በግንባር ቀደምነትነት እንደሚጠቀስ አንስተዋል።
ፖሊስ ከሌብነት እና ከብልሹ አሰራሮች የጸዳ በመሆኑ ለየትኛውም የማህበረሰብ ክፍል በእኩልነትና በታማኝነት የማገልገል ግዴታ ተጥሎበታል ሲሉ አብራርተዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመታገል በየደረጃው የሚገኝ የፖሊስ አባል አጽንኦት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል ብለዋል።
ተቋማችን የሙስና ወንጀልን አጥብቆ የሚጠላ፣ የመልካም አስተዳደር ችግርን የሚያጠፋ፣ በስነ-ምግባሩ የተመሰከረለት ሰራዊትን መገንባት ይገባል ሲሉ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በስርቆት ህብረተሰቡን የሚያስመርር፣ የህዝብና የመንግስት ንብረትን የሚዘርፍ የፖሊስ አመራርም ሆነ አባል ካለ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር በመሆኑ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ የማያዳግም ዕርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።
ትውልድን በስነ-ምግባር ይገነባሉ ተብለው ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከል ፖሊስ ቀዳሚው በመሆኑ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን መጸየፍና መቆጣጠር አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ናቸው።
ሙስና የሀገርን እድገት ወደኋላ የሚጎትት፣ ትውልድን የሚያቀጭጭ በመሆኑ ትውልዱ የስነ-ምግባር እንቅስቃሴ ላይ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በተቋማት ላይ አወንታዊ ተጽዕኖ በመፍጠር ተቋማችን ብሎም ሀገራችን ለሙስና ወንጀል ተጋላጭ እንዳትሆን ፖሊስ ከፍተኛ ስራን ማከናወን ይኖርበታል ሲሉ ምክትል ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
የፖሊስ ዋነኛ ተግባሩ ህዝብን በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን በመጸየፍ ፈፅመው በሚገኙ አካላት ላይም አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ለህግ ማቅረብ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ፖሊስ በስነ-ምግባሩ የታነጸና ሙስናን የሚታገል ከሆነ በህብረተሰቡ ላይ ታማኝነትንና ተቀባይነትን ስለሚያገኝ የወንጀል መከላከል ተግባሩን ያለምንም እንከን ማከናወን ይችላል ሲሉም ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
የፖሊስ ሰራዊታችን እራሱን ከሙስናና ከብልሹ አሰራር ጠብቆ ሌላው የማህበረሰብ ክፍልም ለሙስና እንዳይጋለጥ ተጠናክሮ መስራት ለነገ የማይባል ተግባር ነው ያሉት ደግሞ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ናቸው።
ሙስናን መከላከል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀትና በመደጋገፍ ከሰራን የሙስና ወንጀልን መከላከል እንችላለን ብለዋል።
በፖሊስ ተቋማችን የሙስና ወንጀልና የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅተን እየሰራን ነው ሲሉም ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ወንጀል እና የመልካም አስተዳደር ችግር ፈተና እየሆነ የመጣ ብልሹ አሰራር በመሆኑ ተቋማችን ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
















