በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለፖሊስ አመራሮች እና አባላት የጅኦ ስትራቴጅካዊ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጀምሯል።

በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለፖሊስ አመራሮች እና አባላት የጅኦ ስትራቴጅካዊ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጀምሯል።

በወሎ እና በሸዋ ቀጠና ለሚገኙ የፖሊስ አመራሮች እና አባላት ነው ስልጠና እየተሰጠ የሚገኘው።

በስልጠና መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሐመድ አሚን የሱፍ የክልሉ ፖሊስ እያደረገ ያለው የለውጥ ስራ ክልላችን ከገባበት የፀጥታ ችግር ለመውጣት አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በህግ ማስከበር እና ሰላም ማስጠበቅ ጉዳዮች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነው ሲሉ ከንቲባው አክለው ተናግረዋል።

የክልሉ ፖሊስ ሰራዊትም ከመደበኛ ተግባሩ ባለፈ እየተወጣ ያለው የህግ ማስከበር ስራ አመርቂ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ላቀው በበኩላቸው ክልላችን ከገባበት የጸጥታ ችግር ለመላቀቅ የክልሉ ፖሊስ ያከናወነው የሪፎርም ተግባር እንደ ግብዓት የሚያገለግል ነው ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም ፖሊስ ተቋሙ የፖሊስን የከፍታ ዘመን የሚያጎለብቱ አሰራሮችን እየከወነ በመሆኑ ይህ ስልጠናም የአመራር ብቃትን ለማሳደግና የተከናወነውን የሪፎርም ስራ ተግባራዊነት ለማረጋገጥ የታሰበ መሆኑን ገልፀዋል።

ፖሊስ የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ቆርጦ የተነሳ በአላማው የጸና እንዲሁም ሙያዊ ስነ-ምግባሩን አክብሮ የሚንቀሳቀስ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ቀን እና ሌት ተግባሩን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ አለማየሁ ናቸው።

አቶ በድሉ ውብሸት የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እንደገለጹት የክልሉን ህዝብ ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ ፖሊስ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ያለ እንዲሁም የህዝብ አሌንታነቱንም በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል ለዚህም አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም የተግባር ማሳያ ነው ብለዋል።

ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በበኩላቸው የአማራ ክልል ፖሊስ ከነበረበት ትልቅ ፈተናና ትግል ተነስቶ ወደ ቀድሞ ከፍታው ለመመለስ ይህ ስልጠና ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ተቋሙ እየሰጠ ያለው የስራ ላይ ስልጠና የፖሊስን የከፍታ ዘመን ባጭር ጊዜ የሚያሳይ እና የፖሊስን ተልዕኮ እና አላማ በብቃት ለመፈፀም የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ስልጠናው የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ያካሄደውን የሪፎርም ተግባር አፈጻጸም እና የአመራር ብቃትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ዙሪያ ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top