ዶክተር አንዷለም ዳኜ ላይ የግድያ ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ በ25 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

ዶክተር አንዷለም ዳኜ ላይ የግድያ ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ በ25 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

ተከሳሽ እሱባለው (ሳሙኤል) ነበረ የተባለው ግለሰብ ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 1፡00 – 2፡00 በሆነ ሰዓት ባሕርዳር ከተማ ሰባታሚት ቀበሌ ልዩ ስሙ ቆሼ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ የጦር መሳሪያ ይዞ ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን በሰዓቱ ከባሕርዳር ከተማ ወደ ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲሄድ የነበረውን ዶክተር አንዷለም ዳኜን የያዘውን ንብረት ለመውሰድ እንዲመቻቸው በማሰብ ያሽከረክር የነበረውን መኪና እንዲያቆም ሲጠይቁት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ሁለት ጥይት በመተኮስ ዶ/ር አንዷለም ዳኜን ደረቱን እና ክንዱን በመምታት ገድለውታል።

ስለሆነም ተከሳሹ እሱባለው (ሳሙኤል) ነበረ በፈጸመው የከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ ወይም በአማራጭ የመግደል ወንጀል ፈጽሟል የሚል የመጀመሪያ ክስ ተከሷል።

በተመሳሳይ ጊዜ እና ቦታ ላይ ወደ ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲሄድ የነበረው ዶ/ር በረከት አማረ ላይ ሁለት ጥይት በመተኮስ የመኪናውን ቦዲ በመምታት ተበዳዩን የሳተው በመሆኑ በፈጸመው ከባድ የሆነ ሰው መግደል ሙከራ ወንጀል የሚል ሁለተኛ ክስ ተከሷል።

እንዲሁም በሶስተኛ ክስ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23(3) ላይ የተመለከተውን ተላልፎ ሀሰተኛ የቀበሌ መታወቂያ ሰነዶችን መገልገል ወንጀል ፈጽሟል በሚል በሰሜን ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ ክሶች ቀርበውበታል፡፡

ተከሳሹም የቀረቡበትን ክሶች ክዶ የተከራከረ ቢሆንም ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የባሕርዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዐቃቤ ህግን ማስረጃዎች በመስማት ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ሰጥቶ የመከላከያ ማስረጃዎችን ከሰማ በኋላ ተከሳሹ የቀረቡበትን ክሶች መካለከል አልቻለም።

በመሆኑም በ1ኛው ክስ ስር በወ/ህግ አንቀጽ 671(2) ስ፣ በ2ኛው ክስ በወ/ህግ አንቀጽ 27(1) እና 671(1)(ሐ) ስር፣ እንዲሁም በሶስተኛው ክስ በወ/ህጉ አንቀጽ 378 ስር ድንጋጌዎችን በመቀየር የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቶ፣ የቅጣት አስተያየቶችን በመመርመር ተከሳሹ በአጠቃላይ በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በሙሉ ድምጽ ውሳኔ መስጠቱን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታውቋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top