“ሀገራችን ትላንት ባልተቋጨ፣ ዛሬ በሚተገበር እና ነገን በሚወስኑ የስኬት ጉዞ ላይ ትገኛለች!” ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
‘ከጅኦ ስትራቴጂካዊ ኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና’ በሚል መሪ ሀሳብ ለሁሉም ክልል ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች ስልጠና ተሰጥቷል።
ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በስልጠናው ለተሳተፉ የፖሊስ ሰራዊቱ አመራሮች በቪዲዮ ኮንፈረስ በሰጡት ማጠቃለያ ሀገራችን ኢትዮጵያ ትላንት ባልተቋጨ፣ ዛሬ በሚተገበር እና ነገን በሚወስኑ የስኬት ጉዞ ላይ በመሆኗ ለዚህ ጉዞ መሳካት ሁሉም የፖሊስ ሰራዊት እና ኢትዮጵያውያን መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ተግዳሮቶች ባልተለየበት ያለፋት ሰባት የለውጥ ጉዞ ውስጥ ተጨባጭ ስኬቶችን አስመዝግባለች ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራሉ ባዳና ባንዳዎች የስኬት ጉዟችንን ለመግታት የተለያዩ የሴራ ተግባራትን እየተገበሩ ቆይተዋል ሲሉ አንስተዋል።
በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ሁሉንም የፖሊስ ሰራዊት ያካተተ አሰራር መተግበር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ መሰናክል ለመሆን በሚጥሩ የባዳና ባንዳዎችን እኩይ ሴሬ ማክሸፍ የፖሊስ ሰራዊቱ ጥብቅ ኃላፊነት መሆኑን ነው ኮሚሽነር ጀነራሉ አጽንኦት ሰጥተው ያብራሩት።
እንደ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጻ ብሔራዊ ጥቅም ከግለሰቦች ጥቅምና ፍላጐት የዘለለ፣ ለሁላችንም የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለቀጣይ ትውልድ የምናስተላልፈው ሀገራዊ አደራ በመሆኑ የዚህ አደራ አስረካቢ ባለተራዎች እኛ ነን ሲሉም አክለዋል።
ታሪካዊ ጠላቶቻችን የውስጥ ባንዳዎችን በመያዝ በቀጠናው የጅኦ ስትራቴጂክ የበላይነት ይዘው የቆዩ ቢሆንም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ስኬት የበላይነት ጉዟቸው ተገቷል፤ አሁንም በባህር በር ጥያቂያችን የሚደገም ይሆናል ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራሉ።
ባዳና ባንዳዎች የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ከማስተጓጎል ባለፈ በሉዓላዊነታችን ላይ ለመረማመድ የሚጥሩ በመሆናቸው ፖሊስ ሰራዊታችን ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን ይህን እኩይ ሴራ ማምከን ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል።
የህዝቡን እና የመንግስትን የሰላም ጥሪን ባልተቀበሉ ባንዳዎች ላይ የህግ ማስከበር ስራው ይቀጥላል ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም መሳካት የተጠናከረ፣ የዳበረ እና በስነ-ምግባር የታነጸ የፖሊስ ሰራዊት መገንባትና ለህዝብ ሰላምና ደኅንነት መስዋዕት የሚከፍል ሰራዊት መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
ሰርጎ ገቦችንና ተላላኪዎችን ማጽዳትና ሰላማዊ አማጮችን በማስፋትና ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በማጠናከር ለህዝብ ሰላምና ደኅንነት ተግቶ መስራት ከፖሊስ ሰራዊቱ እንደሚጠበቅም ኮሚሽነር ጀኔራሉ አሳስበዋል።
ከብሔርተኝነት አስተሳሰብ ወደ ህብረ-ብሔራዊ እሳቤ በመሸጋገር እና ከጊዜያዊ አስተሳሰብ ይልቅ ዘላቂና ተራማጅ አጀንዳዎች ላይ በማተኮር ባነገብነው ዓላማ ልክ በመጓዝ በሰራዊታችን አሰራር ፍጹም ከተከለከሉ ዘረኝነት፣ ከሀይማኖት አድሏዊነት፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት እና ከሌብነት መውጣት ይገባል ብለዋል።
በጂኦ ስትቴጂካዊ ቁመናዋ የተከበረች፣ ብሔራዊ ጥቅሟ እና ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ ሀገርን በመገንባት እንዲሁም ለህዝባችን ሰላምና ልማት መረጋገጥ በጋራ መስራት ከሁሉም ፖሊስ ሰራዊት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ሲሉ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በስልጠናው ለተሳተፉ አመራሮች የስራ መመሪያ አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሀገር እንደሀገር ብሔራዊ ጥቅሟና ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ እንድትቀጥል ውስጣዊ ሰላምን ማረጋገጥ ቀዳሚው ተግባር በመሆኑ ይህን ሰላም ማስጠበቅና ማስቀጠል የፖሊስ ሰራዊታችን ኃላፊነት ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስም የክልሉን ህዝብ ሰላም የሚያውኩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ እና እኩይ ሴራቸውን በማክሸፍ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን አስመዝግቧል ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ ህገ-ወጥ ቡድኖች በመንግስት የተሰጣቸውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የተሰጠውን ስልጠና ወደተግባር በመቀየር እና ጆኦ ፖለቲካዊ ሁኔታና ቁመናውን የተረዳ የፖሊስ ሰራዊት በመፍጠር ሀገሪቱ ለጀመረችው የለውጥና የእድገት ጉዞ ትልቅ ኃላፊነት ከሰራዊቱ እንደሚጠበቅ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አሳስበዋል።










