የባንዳነት ተልዕኮ አንግቦ የመጣው የታጠቀ ኃይልና ባንዳውን አጅቦ የመጣው ባዳ ሳይመለስ ቀረ።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምስራቅ ደንቢያ ወረዳ የባንዳነት ተልዕኮ አንግቦ የመጣው የፅንፈኛው ኃይልና ባንዳውን አጅቦ የመጣው ባዳ በሰሜን ምዕራብ ዕዝ ክፍለጦር በተወሰደበት እርምጃ ሙሉ ለሙሉ ተደምስሷል።
የባዳዎችን ተልዕኮ ተቀብሎ ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ የነበረው ህገ-ወጥ ቡድን በተወሰደበት የማያዳግም እርምጃ ከ80 በላይ ተደምስሷል፣ ቁስለኛና ምርኮኛም ሆኗል፤ በርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሳሪያም ተማርኳል።
በተገኘው ድል የተሰማቸውን ደስታ ለመግለፅ እና የድል ባለቤቶቹን የሠራዊት አባላት ለማበረታታ በግዳጅ ቀጠናው የተገኙት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ የደመሰሳችሁትና የማረካችሁት የህገ-ወጥ ስብስብ ባዳ ከሆኑና ከሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብረው የሚሰሩ ባንዳዎች ጭምር በመሆናቸው ባዳዎቹም ሆነ ባንዳዎቹ ቆም ብለው ሊያስቡ እንደሚገባ ትምህርት የሰጠ የማያዳግም እርምጃ ነው ብለዋል።
በባንዳና ባዳው ላይ የተወሰደው እርምጃና የተገኘው አንፀባራቂ ድል የታላቋ ሀገር ሠራዊት መሆናችንና ለኢትዮጵያ ያለንን ክብርና ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ።
ክፍለጦሩ ድል ብርቁ አይደለም ያሉት ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ እንደ ክፍለጦር ከዚህ በፊት ባካሄዳችሁት ስምሪቶች ሁሉ አንፀባራቂ ድል አስመዝግባችኋል።
የዛሬውን ድል ግን ለየት የሚያደርገው በዜሮ ኪሳራ ባንዳዎችንና ተላላኪዎችን በመደምሰስና በመማረካቸው ነው ሲሉም አክለው ተናግረዋል።
እናንተ ዛሬ ተዋግታችሁ ያሸነፈችሁት የኢትዮጵያዊያንን የጀግንነት ወኔና ስነ-ልቦና ተላብሳችሁ፣ ህገ-መንግስታዊ ተልዕኳችሁን ተረድታችሁ በሰለጠነ ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በመታገዝ ያስመዘገባችሁት ድል ወገንን ያኮራ የጠላትን አንገት ያስደፋ አንፀባባራቂ ድል በመሆኑ ልትትኮሩ ይገባል ነው ያሉት።
እንደ መከላከያ ሰራዊት ዘገባ ድሉ መላው የመከላከያ ሠራዊትን የሚያኮራ በመሆኑ ክቡር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዲሁም የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮችን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።
የክፍለጦሩ አዛዥ ኮሎኔል ዘሪሁን ተረፈ በበኩላቸው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ሲንቀሳቀስና የህዝቡን ሠላም ሲያውክ በነበረው ህገ-ወጥ ቡድንና ተላላኪዎቹ ላይ በወሰድንው ጥንቃቄ የተሞላበት ኦፕሬሽን አደረጃጀት:-
02 የብርጌድና የሻለቃ አመራሮችን ጨምሮ 80 በሚሆኑት ላይ ህጋዊ ርምጃ የተወሰደ ሲሆን፣ 30 ምርኮኛና በርካታ ቁስለኛ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም 01መትረየስ፣ 01 ስናይፐር፣ 01 የጦር ሜዳ መነጸር በርካታ የወገብ ትጥቅና የእጅ ቦምብ እንዲሁም የቃታ መሣሪያ መማረኩንና ኦፕሬሽኑ ሰማንያ ለዜሮ በሆነ ውጤት ሰለመጠናቀቁም ገልፀዋል።
ከአመራሮች መካከል ሻምበል አዲሱ መድፉ፣ ሻምበል እንድሪስ አብደላና መቶ አለቃ አህመድ አረጋ ግዳጁን አስመልክተው የተሰጠን ተልዕኮ በህገ-ወጥ ቡድኑ ላይ ርምጃ በመውሰድ የህዝቡን ሠላምና ደኅንነት ማረጋገጥ ነው ብለዋል።
በቀጣይም የቀረውንና ርዝራዥ የጠላት ኃይል በማደንና ርምጃ በመውሰድ የአካባቢውን ሠላም ለማረጋገጥ ዝግጁነታችን ከመቼውም ጊዜ የላቀ ነው ሲሉ አክለው ተናግረዋል።





