“የጀመርነውን ተስፋ ሰጭ የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝብን ሰላም ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ተግባራችን ነው!” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ አመራሮች፣ የክልል ዋና መምሪያ፣ የመምሪያ እና የዋና ክፍል ኃላፊዎች እንዲሁም የዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዦች በተገኙበት በ2018 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሂዷል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በዕቅድ ውይይቱ እንደተናገሩት የጀመርነው ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ፍሬያማ እንዲሆን ተግተን በመስራት የህዝባችንን የሰላም ጥያቄ መመለስ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ ከኩስመና ወደ ከፍታ የጀመርነውን ጉዞ ከግብ ለማድረስ ከማህበረሰባችን ጋር በመሆን ቀን ከሌት መስራት አለብን።
የአማራ ክልል ፖሊስ ሰራዊት ከየትኛውም ሙያዊ ስነ-ምግባርን ከሚጣረሱ ተግባራት በመራቅ በማህበረሰቡ የሚወደድ፣ የሚከበር ግን ደግሞ የሚፈራ ሊሆን ይገባል ሲሉ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
የጀመርነውን ተስፋ ሰጭ የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝብን ሰላም ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ተግባራችን ነው ያሉት አዛዡ የአማራ ህዝብ የአማራ ክልል ፖሊስ ሪፎርምን ይጠብቃል ሲሉ አክለዋል።
ውስጣዊ ተጋላጭነትን መከላከል፣ የውጊያ አቅምን ከፍ አድርጎ የሚመጣውን የትኛውም ኃይል ድል ማድረግ፣ በገለልተኝነት ህዝብ እና መንግስትን ማገልገል፣ የመርማሪዎችን አቅም በማሳደግ ፍትህን ለሚሹ ዜጎች አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት፣ ብልሹ ስነ-ምግባሮችን መቅረፍ እና በቴክኖሎጅ የተደገፉ ስራዎችን መስራት በቀጣይ ትኩረት ይደረግባቸዋል ነው ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)።
በ2017 ዓ.ም የፖሊስ ሰራዊቱ ያስመዘገባቸው እና አሁንም እያስመዘገባቸው ያሉ ወርቃማ ድሎች መኖራቸውን ያነሱት ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የ2018 ዓ.ም ዕቅድን ውጤታማ ለማድረግ ከመቸውም ጊዜ በላቀ ትኩረት መስራት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
ዕቅዱን ያቀረቡት በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የዕቅድ ክትትልና ግምገማ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዘመን ዮሐንስ የተቋሙ የቀጣይ ዓመት ዕቅድ ከክልሉ መንግስት የአምስት ዓመት አሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ የተወሰደ ነው ብለዋል።
በሁሉም ዘርፍ የተሻለ አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ የዕቅዱ ዋና አካል ሲሆን የግዳጅ አፈጻጸም አቅምን ማሳደግ፣ በሎጀስቲክና በስብዕና የተገነባ ሰራዊት መፍጠር እንዲሁም ያላለቁ የሪፎርም ስራዎችን በማጠናቀቅ የህዝብን ሰላም ማረጋገጥ የበጀት ዓመቱ ቀዳሚ ተግባራት መሆናቸውንም ኮማንደር ዘመን ዮሐንስ አስረድተዋል።
የተደራጀ፣ የተጠናከረ እና የተሻሻለ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ስርዓትን ማጎልበት እንዲሁም ቅንጅታዊ ስራን ተግባራዊ ማድረግ በትኩረት ከሚሰሩ ተግባራት መካከል መሆናቸው በዕቅዱ ተመላክቷል።
እንደ ኮማንደር ዘመን ገለጻ የጀልባ ተቆጣጣሪ ፖሊስ ማሰልጠን እንዲሁም የአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁን በማጠናከር የተሻለ የትምህርት ጥራትን ማምጣት የበጀት ዓመቱ ሌላኛው ተግባር መሆኑንም አብራርተዋል።













