“ፖሊሳዊ ስነምግባርን ባከበረ መልኩ የተሰጣችሁን ትልቅ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባችኋል።” ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በቅርቡ ተመርቀው ለመጡ የVIP ጥበቃ ኮማንዶ ተመራቂዎች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ፖሊሳዊ አሰራርን ያከበረ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ የሪፎርሙ አንዱ አካል በመሆኑ ተቋሙ በጥብቅ የከለከላቸውን እና ህጉ የማይታገሳቸውን ቀይ መስመሮችን ባከበረ መልኩ ስራችሁን በአግባቡ በመወጣት እና ሁሉንም ማህበረሰብ በእኩልነት፣ በፍትሐዊነትና በቅንነት ማገልገል ይኖርባችኋል ብለዋል።
የVIP ጥበቃ አለምዓቀፋዊ ሙያ በመሆኑ ልትኮሩ ይገባችኋል ያሉት ኮሚሽነሩ መሪንና ተቋምን መጠበቅ ሀገርን መጠበቅ መሆኑን በመረዳት የተሰጣችሁን ኃላፊነት በብቃት ልትወጡ ይገባል ነው ያሉት።
ኮማንደር አንማው ካሴ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የVIP እና ተቋም ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ ጥበቃ የሚያስፈልገውን አመራር ተቋም የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው መምሪው ከተለያዩ የሰራዊቱ ክፍሎች ተመልምለው እና ልዩ ስልጠና ተሰጥቷቸው የተመረቁ ናቸው ብለዋል።
የVIP ጥበቃ ኮማንዶ ተመራቂዎች በብላቴ ማሰልጠኛ በቂ የክህሎት እና ወታደራዊ ስልጠና ማግኘታቸውን ገልፀው የተሰጠንን ስልጠና እና የስራ መመሪያ ወደ ተግባር በመቀየር የሚጠበቅብንን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።









