በመላው አማራ ክልል ሲሰጥ የቆየው የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዲሁም በባህርዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው 3ኛው ሀገር ዓቀፍ የሐይማኖቶች ጉባዔ በሰላም መጠናቀቅን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አበበ ውቤ በመላው አማራ ክልል ሲሰጥ የቆየው የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል ብለዋል።
በክልሉ ባሉ ሁሉም አካባቢዎች የተካሄደው የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን አንስተዋል።
በ214 ወረዳዎች ፈተናው መሰጠቱን የገለጹት የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዡ በሁሉም የፈተና አካባቢዎች በርካታ የፀጥታ ኃይል መሰማራቱንም አስገንዝበዋል።
በተፈጠረው የፌደራል እና የክልል ጸጥታ ተቋማት ቅንጅት እና የተግባር አንድነት እንዲሁም በህዝቡ ሁለንተናዊ አጋርነት የፈተናው ሂደት በተረጋጋና በተፈለገው ሰላማዊ ሁኔታ መጠናቀቁ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በባህርዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው 3ኛው ሀገር ዓቀፍ የሐይማኖቶች ጉባዔ የጸጥታ ኀይሉ ህዝቡን አጋር አድርጎ ባከናወነው የተጠናከረ ጥበቃ በሰላም ተጠናቋል ብለዋል።
የህዝብ ቅቡልነት ያለው ማንኛውም ዕቅድና ሥራ ሁልጊዜም የሚሳካ መሆኑ ለሌሎች ስራዎች ጭምር ትምህርት እንደተወሰደበት ረዳት ኮሚሽነር አበበ አንስተዋል።
በቀጣይም በአማራ ክልል የሚካሄዱ ሁነቶች በሰላም እንዲከናወኑ አስፈላጊው የፀጥታና ደህንነት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዡ አስታውቀዋል።
የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዲሁም 3ኛው ሀገር ዓቀፍ የሐይማኖቶች ጉባዔ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና መላው ማኅበረሰብ ላደረጉት ሁለንተናዊ ትብብር ምስጋና ያቀረቡት የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዡ ህዝቡ ለሰላሙ መጎልበት የጀመረውን ትብብር እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።

