‘ከኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና’ በሚል መሪ ሀሳብ ለአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች የጂኦስትራቴጂካዊ ስልጠና ተሰጠ።
ስልጠናው ለአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አመራሮች እና አባላት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እና የዋና ጠቅላይ መምሪያው ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ነው የተሰጠው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ለፖሊስ አመራሩ የሚሰጠው የጆኦ ስትራቴጂክ ስልጠና ለወንጀል መከላከል ተግባራት ጠቃሚና ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ተረድቶ ሙያዊ ግዴታውን ለመወጣት ያስችላል ብለዋል።
የሚሰጠው ስልጠና የፖሊስ አመራሩን ለላቀ ተልዕኮ ለማዘጋጀት የሚያስችል መሆኑን ነው ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አክለው የተናገሩት።
በዚህም የክልሉን ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብና ሰላምን ለማጠናከር የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት የሚያስችል መሆኑን ተገንዝቦ ስልጠናውን በአግባቡ መከታተል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በስልጠናው ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የፖሊስ ኀይልን በማጠናከር እና በማደራጀት ብሄራዊ ጥቅምን እና ሉዓላዊነትትን ማስከበር ይገባል ብለዋል።
ለብሄራዊ ጥቅምና ክብር የጸጥታ ኃይሎች ኃላፊነት ከፍተኛ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ሀገራችን ከውጭ ባዳና ከውስጥ ባንዳ በሚገጥማት የጸጥታ ችግር ብትፈተንም በጂኦፖለቲካው ምህዳር ውስጥ ተጨባጭ ስኬቶችን ያስመዘገበች ሀገር ለመሆን ችላለች ነው ያሉት።
እንደ ሀገር በስኬት የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀገራችን በጂኦፖለቲካው ረገድ ያስመዘገበችው ስኬት መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ሀገራችን እያከናወነች ያለችው የልማት ስራዎች ለታሪካዊ ጠላቶቻችን የመቻላችን ማረጋገጫዎቻችን ናቸው ብለዋል።
የክልሉን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስና የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ በሚደረገው ህግ የማስከበር ተግባር የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ከመከላከያ ሰራዊትና ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በመስዕዋትነት የታጀበ ገድል እየፈፀመ ነው አሁንም የህግ ማስከበር ስራዎቻችን የተረጋገጠ እና አስተማማኝ ሰላም እስከሚመጣ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያስታወቁት።
ስልጠናውን የሰጡት ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ብርሀኑ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሰው ኃብት ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሀገራችን ሰላምና ልማት እንዲስተጓጎል በቀጥታም ይሁን በተላላኪ ባንዳዎች ዕኩይ ተግባራትን እየተገበሩ መሆኑን ገልጸው ይህም ሴራ በጸጥታ ኃይሉ እና በህዝቡ ጥረት የሚከሽፍ ይሆናል ብለዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ብርሀኑ ገለጻ የሀገራችን የጸጥታ ኃይል የመጨረሻ ዓላማና ግቡ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ፣ ብሄራዊ ጥቅሟ የተከበረ፣ ሰላማዊ ሀገርን መገንባት በመሆኑ ‘ከኩስመና ወደ ተሻለ ቁመና’ ለምናደርገው ጉዞ ወሳኙን ሚና ይይዛል ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
የሀገራችን የጸጥታ ሀይል 2/3ኛ የሚሆነውን የሀገሪቱን ኃላፊነት የተሸከመ ነው የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ለሀገራችን ሉዓላዊነት መከበርና ብሄራዊ ጥቅም መጠበቅ ተላላኪዎችንና ባንዳዎችን ማጽዳት፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ባለቤታዊ ተሳትፎ ማድረግ እና የህዝብን ሰላም ማስጠበቅ ከፖሊስ ከሚጠበቁ ኃላፊነቶች መካከል በቀደምትነት ይጠቀሳል ሲሉ ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ብርሀኑ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሰው ኃብት ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አብራርተዋል።








