የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የ2018 ዓ/ም የመጀመሪያ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸምን ገመገመ።
የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የአፈጻጸም ግምገማ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥን ጨምሮ ምክትል ኮሚሽነሮች፣ የዋና መምሪያ፣ የመምሪያ እና የዋና ክፍል ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
የአፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡት ኮማንደር ዘመን ዮሐንስ የዕቅድ ክትትልና ድጋፍ መምሪያ ኃላፊ እንዳስታወቁት ዋና ጠቅላይ መምሪያው የፖሊስ ተቋሙን ዘመናዊ፣ ህዝባዊ እና ገለልተኛ ለማድረግ እየተገበረ ባለው ሁለንተናዊ የሪፎርም ሂደት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።
በሩብ ዓመቱ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመቆጣጠር እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የፖሊስ አመራሮችና አባላት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ድንበር ዘለል ወንጀሎችን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ከአጎራባች ክልሎች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች ጋር የነበረው በቅንጅታዊ አሰራር በቀረበው ሪፖርት በመልካም ጎን ተመላክቷል።
ከሀገር ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት እንዲሁም ከክልሉ አጋር የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን በተሰራው ቅንጅታዊ ስራ በህገወጥ ቡድኖች ላይ አየተወሰደ ያለው ህግን የማስከበር ተግባር እና በክልሉ የተከወኑ ሁነቶች ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ ማድረግ መቻሉ በጥንካሬ ተጠቅሷል።
የአድማ መከላከል ፖሊስ ኃይሉ ስነ-ምግባርን ተላብሶ የመዋጋት አቅሙን እና የግዳጅ አፈጻጸሙን ለማሳደግ በአራት ቀጠናዎች ከአጋር አካላት ጋር እና በተናጠል በተሰማራባቸዉ ግዳጆች ጠንካራ ዉጤት እያስመዘገበ እንደነበር በሪፖርቱ ተገልፃል ፣ በተጨማሪም የስራ ላይ ስልጠና መሰጠቱ በሩብ ዓመቱ ከተከናወኑ አንኳር ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ስኬቶች መሆናቸዉ ተገልጿል።
ጤናማ የመንገድ ትራፊክ ፍሰት እንዲኖር የትራፊክ ፖሊሶች ከአጋር አካላት ጋር ባከናወኑት ተግባር የተሻለ አፈጻጸም መመዝገብ መቻሉም ተመላክቷል።
በወንጀል ምርመራ ስራዎች 3876 ልዩ ልዩ የወንጀል ጥቆማዎች ለፖሊስ መድረሱን ያነሱት ኮማንደር ዘመን 3215ቱ የምርመራ መዝቦች ተጠናቀው ለዐቃቤ ህግ መላካቸውን እንዲሁም 593ቱ መዝቦች በሂደት ላይ እንዳሉ፤ 68ቱ ደግሞ በልዩ ልዩ ምክነያቶች መቋረጣቸውን ነው ኮማንደር ዘመን በሪፖርቱ አክለው ያስታወቁት።
የፖሊስን የመፈጸም ብቃት ለማሳደግ ታስቦ ባሰተዳደር ልማት በሪፎርም ስራዎች ዙሪያ በተመለከተም የተለያዩ ሰነዶች እና ጊዜያዊ የሰው ኃይል ምደባ መመሪያ እና ስታንዳርድ ተዘጋጅቶ በኃላፊነት ምደባ ላይ በተሰራው ስራ አበረታች ውጤት ማምጣት፣ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እና የአሰራር ቅልጥፍናን ለመፍጠር ያለመ የዲጂታላይዜሽንና የለውጥ ስራዎች በሩብ ዓመቱ ተስፋ ሰጪ ስራዎቸ ተጀምሯል ብለዋል።
ቀጠናዎችን ተከፋፍለው ለሰራዊቱ ድጋፍ በመስጠት እና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ ስትራቴጂክ አመራሮች ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ተገልጿል።
በአማራ ክልል ፖሊስ የተከናወኑ ተግባራትን ለህዝብ እና ለሰራዊቱ ተደረሽ እንዲሆኑ የፖሊስ ሚዲያ የሰራው ስራ እንዲሁም በክልሉ የተከናወኑ ሁነቶችን በማድመቅ እና በማጀብ በኩል የፖሊስ ማርች ባንድ እና የኪነት ቡድኑ ያከናወኑት ተግባር በኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ከፈጸማቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በአጠቃላይ ፖሊስ በሕዝብ ቅቡልነት ያለው እና የዜጎችን ደህንነት የሚያረጋግጥ ተቋም እንዲሆን በትኩረት ተሰርቷል ሲሉ ነው ባቀረቡት ሪፖርት ያብራሩት።
በቀረበው ሪፖርቱ ላይ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ሀሳብ እና አስተያየት አንስተዋል።
ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥን በሰጡት ማጠቃለያ ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ የጀመረውን የለውጥ ስራ በሁለንተናዊ መልኩ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለውጡ መሰረተ ልማትን እና ቴክኖሎጂን ከመገንባት ባለፈ የህዝብን እምነት እንደገና በመገንባት፣ ዜጎችን በመጠበቅ፣ ፍትህን በማስፈን እና ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ላይ ማተኮር እንዳለበትም ገልጸዋል።
ከፍትህ ተቋማት ጋር የጀመርነውን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክረን የወንጀል ምርመራ ስራን በማሳደግ በክልሉ ፍትህ እንዲረጋገጥ የበኩላችንን ድርሻ ልናበረከት ይገባል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ በማብራሪያቸው።
እንደ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ በጎ የሆነ የውድድር መንፈስን በመፍጠር የተሻለ የስራ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ቀን ከሌት ልንሰራ ይገባል።
የሚሰጠውን ተልዕኮ እና ግዳጅ በአመርቂ ውጤት መፈጸም የሚችል የፖሊስ ኃይል መፍጠር ይጠበቅብናል ሲሉ ነው ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።
ለፖሊስ ሰራዊቱ ተከታታይነት ያለው የስራ ላይ ስልጠናዎችን በመስጠት እና አቅሙን እንዲያጎለብት በማድረግ የአማራን ህዝብ ሰላም እና ደኅንነት በቁርጠኝነት የሚጠብቅ ኃይል ለማድረግ ተግተን መስራት ይገባል ብለዋል።
ቅንጅታዊ አሰራራችን በተገቢው መንገድ አጎልብተን የምናስመዘግበው ውጤትም ሆነ ውድቀታችን የጋራ መሆኑን በመገንዝብ በቡድን የመስራት ልምዳችን ማሳደግ እንደሚገባ ነው ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አጽንኦት የሰጡት።
የአፈጻጸም ግምገማ መድረኩ በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ነጥቦች ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል።































