ለስትራቴጅክ እና ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች የተሰጠው ስልጠና ተጠናቀቀ

ለስትራቴጅክ እና ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች የተሰጠው ስልጠና ተጠናቀቀ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለስትራቴጅክ እና ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሲሰጥ የነበረው የአመራርነት ስልጠና ተጠናቀቀ።

ስልጠናው የፖሊስን የአመራር ብቃት ማሳደግ፣ ወቅታዊ የፀጥታ ችግሮችን በብቃት መወጣት እንዲችሉ ማስቻል እንዲሁም በተቋማዊ ሪፎርም፣ በስነ ምግባር እና በለውጥ አመራርነት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ነው።

በማጠቃለያ መርሀ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የፖሊስን የማስፈጸም አቅም የሚያጎልበት ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል።

የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የሚቻለው በፖሊስ ተቋም ውስጥ ጠንካራ አመራር በመፍጠር መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉን ህዝብ ከችግር የሚያወጣ እና ህዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በጥሩ ስነ-ምግባር መስጠት ይኖርባችኋል ሲሉም ለአመራሮች አሳስበዋል።

ዕርስ በዕርስ የሚናበብ እና የሚግባባ የፖሊስ ኃይል ለመገንባት የጀመርነውን ሪፎርም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

እንደ ኮሚሽነር ዘላለም (ዶ/ር )ገለጻ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች ከስልጠናው ያገኙትን የአመራርነት ጥበብ በመጠቀም ማህበረሰቡን የጸጥታው ባለቤት በማድረግ በቅድመ ወንጀል መከላከል ተግባር ላይ አተኩረው ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጡም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መስፍን አበበ የፖሊስ አመራር ተከታታይነት ያለው ስልጠና በመውሰድ ከቴክኖሎጂ ጋር የተላመደ ብቁ አመራር ሆኖ መገኘት አለበት ብለዋል።

ፖሊስ ዘመኑን ቀድሞ መተንበይ እና የአመራር ስልቶችን መቀየስ የሚችል ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

ዩኒቨርሲቲው ለክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና ለአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መስፍን ገልጸዋል።

በስልጠናው የተሳተፉ የፖሊስ አመራሮች ስልጠናው በሙያቸው ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያግዛቸውን ዕውቀትና ክህሎት እንዳገኙበት ገልጸዋል።

ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ በትጋት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ስልጠናው የተቋሙን ተልዕኮ መነሻ በማድረግ የተካካሄደ ሲሆን በቀጣይ መሰል የስራ ላይ ስልጠናዎች በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና አባላት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረው ሪፎርም ከግብ እንዲደርስ እና አመራሩ ጊዜው የሚጠይቀውን እውቀት እንዲላበስ ላደረጉት አስተዋጽኦ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)ምስጋና አቅርበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top