
ታማኝነቷን ያስመሰከረችው ኢንስፔክተር ሰላም
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የዝቋላ ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት መንገድ ትራፊክ ደህንነት ክፍል ኃላፊ የሆነችው ም/ኢ/ር ሰላም መኮነን ሚያዚያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ረፋድ ላይ በባንክ ሂሳብ ቁጥሯ በስህተት 140,000/አንድ መቶ አርባ ሺ/ ብር ገቢ ሆነ።
ገንዘቡ የእሷ አለመሆኑን የተረዳችው ም/ኢ/ር ሰላም ለኃላፊዋ በስልክ ወዲያውኑ በማሳወቋ የገንዘቡ ባለቤት ሲጣራ የዝቋላ ወረዳ 01 ቀበሌ ፅፅቃ ከተማ ነዋው ደሳለኝ ኪሮስ መሆኑ ተረጋግጧል።
የዝቋላ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤትም ደሳለኝ ኪሮስን ወደ ቢሮ አስጠርቶ በአደረገው ማጣራት ገንዘቡን ለንግድ ትስስር ላለው ግለሰብ በሞባይል መተግበሪያ ሲያስተላልፍ በስህተት 140,000(አንድ መቶ አርባ ሽህ ) ማስተላለፍን ገልፆ ገንዘቡ ለጠቀሰው ግለሰብ አለመድረሱን ሲያውቅ ተጨንቆ እንደነበር ገልጿል።
ም/ኢ/ር ሰላምም የገንዘቡን ባለቤት ደሳለኝ ኬሮስ መሆኑን ከተረጋገጠ በኋላ 140,000 ብሩን የመለሰች ሲሆን ወጣት ደሳለኝ ኪሮስም ገንዘቡን በማግኘቱ አመስግኗል።