
የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ያሰለጠናቸውን የመደበኛ ፖሊስ አባላትን አስመርቋል።
ለአንድ ሀገር ልማትና እድገት መረጋገጥ አስተማማኝ የሰላም ሁኔታ እና አስተማማኝ የፀጥታ ኀይል የመኖር አስፈላጊነት የሚያጠራጥር አይደለም።
የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ በብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸውን የ33ኛ ዙር መደበኛ ፖሊስ አባላትን አስመርቋል።
በምረቃ ዝግጅቱ ላይ ሜጀር ጀነራል ግዛው ኡማ የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ፣ ረዳት ኮሚሽነር አበበ ደለለ የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር፣ ኮሎኔል መኮንን መንግስቴ የብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ፣ ኮማንደር አብዮት ሽፈራው የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው ኃብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኀላፊ እንዲሁም የፖሊስ እና የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተዋል።
ረዳት ኮሚሽነር አበበ ደለለ የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር የአማራ ክልልን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር እንዲሁም ለህዝብ፣ ለሀገር፣ ለመለዮና ለአርማ እስከ ህይወት መስዕዋትነት ለመክፈል የተዘጋጁ የመደበኛ ፖሊስ አባላት ሠልጥነው መመረቃቸውን ገልጸዋል።
ወንጀል ፈጻሚዎች በህዝብ ላይ በደል እንዳይፈፅሙ ቆርጦ በመነሳት እና በመፋለም ሰላምን ማጽናት ይገባል ብለዋል።
እንደ ረዳት ኮሚሽነር አበበ ገለጻ በክልላችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመከላከል ኀላፊነታችሁ ድርብ በመሆኑ የወሰዳችሁትን ስልጠና ተጠቅማችሁ እንዲሁም ከሌሎች የፀጥታ ኀይሎች ጋር በጋራ በመሆን ህዝብ እና ሀገርን መታደግ ይገባችኋል።
የአንድነት መጓደል ተገርስሶ ወደ ሰላምና ልማት ለመሸጋገር ተስፋ የሰጠ ስልጠና መሆኑን የገለጹት ረዳት ኮሚሽነሩ የክልላችን ሰላም በራሳችን ጣምራ ክንዶች እና መስዋዕትነት ማስከበርና ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።
እናንተ የዛሬ ተመራቂ የመደበኛ ፖሊስ አባላት በተግባር እና በንድፈ-ሀሳብ ስልጠና የወሰዳችሁትን ፖሊሳዊ ሳይንስን በመላበስና በጽናት በመፋለም አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የአማራን ህዝብ ሰላም በማረጋገጥ በታሪክ ልትመዘገቡ ይገባል ብለዋል።
በስልጠናው ብቁ መሆናችሁ የሚረጋገጠው ወደስራ ስትሰማሩ ባስመዘገባችሁት ውጤት የሚለካ ነው ያሉት ረዳት ኮሚሽነር አበበ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ያለአድሎ ህዝብን ማገልገል ይገባል ሲሉ አክለዋል።
የፀጥታ ኀይል ለተሰጠው ተልዕኮ እና ኃላፊነት እንዲሁም ህዝብን ለማገልገል እስከ ህይወት መስዋዕትነት መክፈል ይጠበቃልና ለዚህም ዝግጁ መሆን እንደሚገባ ረዳት ኮሚሽነር አበበ ደለለ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ለስልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።




