“የክልሉ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት እውን እንዲሆን የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፉ የማይተካ ሚናውን መወጣት ይኖርበታል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

“የክልሉ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት እውን እንዲሆን የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፉ የማይተካ ሚናውን መወጣት ይኖርበታል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

የአማራ ክልል የዳኝነት እና ፍትሕ ዘርፍ የ5 ዓመታት የልማት እቅድ ዝግጅት ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ከክልሉ የ25 ዓመታት ዕድገት እና ዘላቂ ልማት እቅድ የተቀዳው የመጀመሪያው የ5 ዓመታት እቅድ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት የእቅድ ዝግጅቱ ረቂቅ ቀርቦም ግብዓት ተሰጥቶታል፡፡

ከአማራ ክልል የ25 ዓመታት ዕድገት እና ዘላቂ ልማት እቅድ ጋር ተጣጥሞ የሚዘጋጀው የዳኝነት እና ፍትሕ ዘርፉ የ5 ዓመታት ዕቅድ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝነት አለው ተብሏል።

ለርእሰ መሥተዳድሩ የቀረበውን ረቂቅ ዕቅድ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የአማራ ክልል ማረሚያ ፖሊስ አመራሮች ግብዓት ሰጥተውበታል፡፡

ረቂቅ እቅዱን ለተወያዮቹ ያቀረቡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው እቅዱ የሕግ የበላይነትን እና የዳኝነት ነጻነትን፣ የላቀ የፍትሕ አገልግሎትን፣ የፍትሕ ተደራሽነትን እና ሰብዓዊ መብትን በትኩረት የዳሰሰ ነው ብለዋል፡፡ እቅዱ ሙያዊ ነጻነትን እና የተቋማትን ገለልተኛነት አስጠብቆ ዘላቂ ሰላም፣ ፍትሐዊ ልማት እና ሁለገብ እድገትን ለማረጋገጥ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የእቅድ ዝግጅቱ ሂደት ተቋማት ለጋራ ግብ በቅንጅት መሥራትን ያለማመደ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እቅድ ዝግጅቱ አሁናዊ ችግሮቻችን እና የቀጣይ ጊዜ ፍላጎቶቻችንን ያጣጣመ መኾን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ እቅዱም መነሻ ያለው፣ ግልጽ፣ የሚለካ እና የሚደረስበት መኾኑን ደጋግሞ ማረጋገጥ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የክልሉ የመልማት እና ዕድገት ፍላጎቶች እውን እንዲኾኑ ከተፈለገ የዳኝነት እና ፍትህ ዘርፉ የሚጠበቅበትን መወጣት አለበት ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “በዘላቂነት ከግጭት አዙሪት የምንወጣው የፍትሕ ሥርዓቱን ማሻሻል ስንችል ነው” ብለዋል፡፡ የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓቱ እንዲሻሻል ደግሞ አቅዶ እና አልሞ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ረቂቅ እቅዱን ለማዘጋጀት የተደረገውን ጥረትም ርእሰ መሥተዳድሩ ማድነቃቸውን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በማህበራዊ ትስስር ገፁ አስነብቧል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top